በሃገር አቀፍ ደረጃ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በማህበረሰቡ ላይ እያደረሱ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት ባህል እና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በጋራ በመሆን ጤናማ ባልሆኑ ምግቦች የአመጋገብ ስርዓት ምክንያት የሚከሰቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አስመልክቶ ምክክር አካሂዷል፡፡

በመርሃግብሩ የተሳተፉ የቋሚ ምክር ቤቱ አባላት ማህበረሰባችን ስለ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ የተለያዩ መንገዶች በመጠቀም ግንዛቤውን ከፍ ለማድረግ በተገቢው መንገድ መሰራት እንዳለበት ተናግረው የሚመለከታቸው አካላት በትብብር መስራት እንዳለባቸውም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ ስለጤናማ ያልሆኑ ምግቦች ምንነት፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያስከትሉትን ውስብስብ የጤና ችግር እንዲሁም የታሸጉ ምግቦችን አስመልክቶ ሃገራዊ ህጎቻችን አሁናዊ ሁኔታ የሚገልጹ ጥናቶች በባለሙያዎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

በመጨረሻም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት ባህል እና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበርም የጀመረውን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል የቋሚ ኮሚቴው አባላት አሳስበዋል፡፡