ጎንደር ምንጭ፡ #አስቻለው አባይነህ
ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እ.ኤ.አ ታህሣስ 15/1971 በጐንደር ከተማ ተወለዱ፡፡ የአንደኛ፣ የመካከለኛ ሁለተኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጐንደር ህብረት፣ አፄ በካፋ እና ፋሲለደስ ትምህርት ቤቶች እኤአ ከ1976 እስከ 1987 ባሉት ጊዜያት አጠናቀዋል፡፡
እኤአ በ1995 ከጅማ ዩኒቨርስቲ በጠቅላላ ሀኪምነት ከተመረቁ በኋላ እንደገና እኤአ በ2003 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሜዲካል ፋኩልቲ በጠቅላላ ቀዶ ህክምና በስፔሻሊስት ደረጃ ተመርቀዋል፡፡እኤአ በ2013 ደግሞ በልብ ቀዶ ህክምና በተለየ ሙያ ሠልጥነው ተመርቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በመንፈሳዊ ትምህርት ከኢትዮጵያ የቲዮሎጂ ትምህርት ቤት በማስተርስ ደረጃ ተመርቀዋል፡፡
ዶ/ር ብርሃኑ በአዲ-አርቃይ ጤና ጣቢያ እኤአ ከ1995 እስከ 1996 የህክምና ሙያ ስራቸውንና የጤናውን ተግባር በወጣትነታቸው የማስተባበሩን ሥራ አሀዱ ብለው ይጀምሩ እንጂ ከዚያም በፊት በነበራቸው የኮሌጅ ቆይታቸው የመጨረሻ አመታት በተለያዩ ቦታዎች ከሙያቸው ጋር ያላቸውን ቅርበትና ዝምድና ፈትሸዋል፡፡

ዶ/ር ብርሃኑ በጅማ ዩኒቨርስቲ በምክትል ወይም ረዳት አስተማሪነት በቀዶ ህክምና መምሪያው ውስጥ እኤአ ከ1996 እስከ 1997 ባለው የአንድ ዓመት ቆይታቸው የጀመሩትን ተግባር በማጠናከርና ወደ ሙሉ መምህርነት ከፍ በማድረግ ብዙ ሙያተኞችን አፍርተዋል፡፡
ከዚያም ወዲህ ባሉት ዓመታት በረዳትና በተባባሪ የፕሮፌስርነት ማዕረግ በጅማ ዩኒቨርስቲ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በዋናነት የቀዶ ህክምና ክፍሎችን በኃላፊነት እየመሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሰርጂካል አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመሆንና የኢትዮጵያ ህክምና ባለሙያዎች ማህበር ምክትል ፕሬዘዳንት ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡
ዶ/ር ብርሃኑ ከ18 በላይ የጥናት ውጤቶችን በተለይ ክልብ ቀዶ ጥገና፣ ከትልቁ አንጀት፣ ከፊንጢጣ እና ከመሳሰሉት በሽታዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር አያይዘው በማከናወን በተለያዩ ጆርናሎች ላይ እንዲታተሙ ያደረጉ ብርቱ ሰው ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ በተለያዩ ሙያዊና እንዲሁም አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተሣትፏቸው ከ30 በላይ ሰርቲፊኬቶችን ያገኙ ሲሆኑ በሁሉ ቦታ ያለ ዕረፍት ሙያዊ ግዴታቸውን በመወጣትና የማስተባበር ሚናቸውን በማጐልበት ላይ ያሉ ጠንካራ የህክምና ጠቢብ ናቸው፡፡