በዶክተር ታዘባቸው ጉዳይ በኢትዮጵያ ህክምና ማህበር የተሰሩ ስራዎችን አስመልክቶ የተሰጠ መረጃ

የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር በተማሪ ቢኒያም ኢሳያስ ጉዳይ ላይ ከመጋቢት 26 ቀን 2014ዓ.ም ጀምሮ ሲሰራ የቆየ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪ የህክምና ትምህርቱን እንዲጨርስና እና የድህረ ምረቃ ትምህርት ለመከታተል የሚያስችል ድጋፍ እንዲደረግለት ከጤና ሚኒስቴር፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ጋር ባደረግነው ውይይት ሞያዊ ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል ።

የዶ/ር ታዘባቸው ውዴ ጉዳይን አስመልክቶም በቅርበት በመከታተል ከተለያዩ አካላት ጋር በጋራና በተናጠል ባለጉዳዩን (ዶ/ር ታዘባቸው ውዴን) ጨምሮ ውይይት አድርገናል፡፡ ባደረግናቸው ውይይቶችም ሞያዊ ምክረ ሃሳቦችን ያቀረብን ሲሆን በተለይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሎጅ እንዲሁም ከጽንስና ማህፀን ህክምና ትምህርት ክፍል ጋር ባደረግነዉ ስብሰባም ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በሚረዳ መልኩ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስና መምህርና ተማሪ እንዲሁም ሐኪምና ታካሚ መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲኖር በቀጣይም መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱ መሰረታዊ ስራ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ተረድተናል፡፡

ማህበሩ ከሁሉም አጋር አካላት ጋር ካደረገው ውይይት በመነሳት ከህክምና ትምህርት ቤቶች፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የሐኪሞችን መብትና ደህንነት፣ የህክምና ትምህርት የመግቢያ ፈተና መስፈርቶችን እና የታካሚዎችን ደህንነት እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች እና የቴክኖሎጂ እድገቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ለመግለጽ ይወዳል፡፡

ማህበሩ የህክምና ሙያ አካል ጉዳተኞችን ያካተተ መሆን አለበት ብሎ ያምናል። ለዚህም አካል ጉዳተኞችን በህክምና ትምህርት ዘርፍ እንዲሳትፉ በማድረግ አካታች የትምህርት ስርዓትን ከመፍጠርም ባሻገር የጤና ስርዓቱንም አካታች (disability inclusive health care system) ከመፍጠር አንፃር ጉልህ አስተዋፅኦም ይኖረዋል ብሎ ያምናል፡፡ በመሆኑም ማህበሩ በዚህ ጉዳይ ላይ ሃገሪቱ የፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲኖራትም ከሚመለከታቸዉ አካልት ጋር እየሰራ ይገኛል፡፡

ለማህበሩ አባላት የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር የሐኪሞችን መብትና ጥቅም ከማስከበር አኳያ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር መስራቱን እንደሚቀጥል እያረጋገጠ የዶክተር ታዘባቸው ጉዳይን በቀጣይ የደረስንበትን የምናሳውቅ መሆኑን ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡