የሀዘን መግለጫ

ዶ/ር ጫላ ኢዶሳ በአምቦ ወረዳ ቁርቢ ቀበሌ ከአባታቸው አቶ ኢዶሳ ሞገሴ እና ከእናታቸው ወ/ሮ አገሪ ገመቹ በ1982ዓ.ም ተወለዱ::
እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በሜጢ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በመቀጠልም በአምቦ አንደኛና መለስተኛ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል:: ከዘጠነኛ እስከ አስራሁለተኛ ክፍል ትምህርታቸውን በአምቦ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት አጠናቀው በመሰናዶ መለቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ በአዳማ ዩንቨርሲቲ ህክምና ትምህርት ቤት ተመድበው ከ2002-2008ዓ.ም የህምና ትምህርታቸውን በመከታተል በ2008ዓ.ም በህክምና ዲግሪ ተመርቀዋል::

ከ2008ዓ.ም እስከ 2009 ዓ.ም በአዳማ ዩንቨርስቲ ህክምና ኮሌጅ አሰላ ሆስፒታል ተቀጥረው በመምህርነት እና በጠቅላላ ሀኪምነት ያገለገሉ ሲሆን ከ2010ዓ.ም ጀምሮ የቀዶ ጥገና ህክምና ስፔሻሊቲ ትምህርታቸውን እየተማሩ ለአሰላ እና አካባቢዋ ህብረተሰብ በህክምና ሞያቸው የላቀ አስተዋፆን አበርክተዋል::

ዶ/ር ጫላ ኢዶሳ

ዶ/ር ጫላ በባህሪያቸው ሰው አክባሪ፣ለሰው አዛኝ ፣ ትሁት ፣ተግባቢ እንዲሁም በስራቸው ታታሪ ለሞያቸው ታማኝ በትምህርታቸውም በጣም ጎበዝ የነበሩ ሲሆን ሰኔ 28/2013ዓ.ም በተወለዱ በ31 ዓመታቸው በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል::የቀብር ስነስርአታቸውም ሰኔ 30/2010ዓ.ም በትውልድ ቦታቸው አምቦ ሜጢ ቀበሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል::

የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር በዶ/ር ጫላ ኢዶሳ ህልፈት ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸው ለጏደኞቻቸው ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም ለስራ ባልደረቦቻቸው መፅናናትን ይመኛል::