የሀዘን መግልጫ

ዶ/ር ኤልሳቤት መኮንን ከአባታቸው ከአቶ መኮንን ግርማይ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ላዛ አበራ በሱዳን ሀገር በ1983 ዓ.ም ተወለዱ:: እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመምጣት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ክፍል በሽመልስ ሀብቴ ት/ቤት ፣ ከአራተኛ እስከ ዘጠነኛ ክፍል በብሉ በርድ ት/ቤት ያጠናቀቁ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በልደታ ካቶሊክ ካቴድራል ት/ቤት አጠናቀዋል::

በመቀጠልም የሀገር አቀፍ የ12ተኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምና ትምህርት ለመማር ተቀላቅለዋል:: በህክምና ትምህርት ቤት ቆይታቸው ከብዙ ተማሪዎች ጋር እጅግ የቀረበና ፍቅርን የተሞላ ጏደኝነት የነበራቸው ፣ በአስተማሪዎቻቸውም ዘንድ ተወዳጅነት የነበራቸው ታታሪ: ሩሁሩህና ፍቅርን የተላበሱ ሀኪም በመሆን በ2009 ዓ.ም በህክምና ዶክትሬት ተመርቀዋል::በተማሩበት የህክምና ትምህርት ሀገርን እና ህዝብን ለማገልገል በኦሮሚያ ክልል አዶላ ከተማ በመንግስት እና በግል ሆስፒታል ለአራት አመታት ሲያገለግሉ ቆይተዋል ::

ዶ/ር ኤልሳቤት መኮንን

ዶ/ር ኤልሳቤት መፅሀፍ ማንበብ በእጅጉ የሚወዱ ፣ ከሞያቸው ውጪ አዳዲስ የስራ ሀሳቦችን ለማምጣትና ለመሞከር ከፍተኛ ተነሳሽነት ያላቸው ፣ ለተፈጥሮ ካላቸው ልዩ ፍቅር የተነሳ አትክልቶች በመትከልና በመንከባከብ የሚታወቁ ፣ ህፃናትን በእጅጉ የሚወዱ ፣ ደግነትና ለጋስነትን ከተረፋቸው ብቻ ሳይሆን ካላቸው ቀንሰውና ተበድረው ለሰው በመቆረስ ያስተማሩ ፣ የታካሚዎቸውን ብቻ ሳይሆን የሰው ሁሉ ችግር አይተው ማለፍ የማይችሉ – ለአዶላ ከተማ ህዝብ ተምሳሌት መሆን የቻሉ ሩህሩህና ተወዳጅ ሀኪም ነበሩ:: 

ዶ/ር ኤልሳቤት መኮንን ለአራት አመታት ባገለገሉበት በአዶላ ከተማ ታህሳስ 30, 2013 ዓ.ም በድንገት በመኖርያ ቤታቸው ውስጥ ህይወታቸው አልፉል::የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር በዶ/ር ኤልሳቤት ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ ለቤተሰባቸውና ለወዳጆቻቸው ሁሉ መጽናናትን ይመኛል፡፡