የሕክምና አገልግሎት ለሚሰጡ ሐኪሞች በነጻ ሕክምና ሊያገኙ የሚችሉበት ስርዓት እንዲኖር ተጠየቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር ለስድስተኛ ጊዜ የሚከበረውን የሐኪሞችን ቀን የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ 100ኛ ዓመት ከሚያከብረው ኦፒዲ ዳይሬክቶሬት ጋር በመሆን የሆስፒታሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የሆስፒታሉ ባለሙያዎች እንዲሁም የማህበሩ የቦርድ አባላት በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ውሏል፡፡

የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ኘሮቮስት ዶክተር ኤልያስ ተዋበ ባስተላለፉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በሆስፒታሉ ስለሚሰጡ ዋና ዋና አገልግሎቶች የገለጹ ሲሆን የአገልግሎቶችን ጥራት አስጠብቆ ማህበረሰቡን ለማገልገል በትብብር መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ ሕክምና የቡድን ስራ እንደመሆኑ መጠን የሐኪሞች ቀን በሆስፒታሉ ለማክበር ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡን በሚጠቅም መልኩ ታስቦ እንዲውል በማሰብ ከሆስፒታላችን ጋር በጋራ ለማክበር እዚህ በመገኘታችሁ ደስታ ይሰማናል ብለዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የጤና ዘርፍ የሰው ሃብት ልማትና ማሻሻያ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ አሰግድ ሳሙኤል የጤና ሚኒስቴር ባለሙያዎች ለማትጋት የተለያዩ አማራጮችን እንደሚጠቀም አስታውሰው የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ የማይተካ ሚና ያለውን ብቃት ያለው ባለሙያ ለማፍራት ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ ባለሙያው ለሰራቸው ስራዎች በሚከበርበት ቀን ተገኝቶ ማመስገን ይገባል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ሐኪሞች ከሌሎች የጤና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ለሚሰሩት ስራ ለማመስገን፣ ለማበረታት፣ እውቅና ለመስጠትና በቀጣይም የሚጠበቁብንን ኃላፊነቶች በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችል አቅም ለማዳበር እንዲህ ያሉ መርሃግብሮች ጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ተግባር ይግዛው የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር ፕሬዝደንት በበኩላቸው የሆስፒታሉን 100ኛ ዓመት ከማክበር በተጨማሪ ማህበሩ የሐኪሞችን ቀን በጋራ ለማክበር ያደረገውን ጥሪ የሆስፒታሉ አስተዳደር በመቀበሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

አክለውም የሐኪሞች ቀን ችግሮቻችን ብቻ ሳይሆን ለማህበረሰቡ ለሃገር ያደረግነው በጎ ነገር የምንዘክርበት ነው ያሉ ሲሆን፤ ሰው ሲታመም የሚያክም ሐኪሙ እሱ ስታመም በፌስቡክ መለመን የለበትም፤ ሕክምና ለሚሰጡ የሕክምና ባለሙያዎች በነጻ ሕክምና ሊያገኙ የሚችሉበት ስርዓት እንዲኖር መስራት ያስፈልጋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የማህበሩ የዘንድሮ መሪ ቃላችን ነጻ ሕክምና ለሐኪሙ/ሟ እንደሆነም ዶ/ር ተግባር በንግግራቸው አስታውሰዋል፡፡