የማህበሩ መግለጫ

የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር አንገብጋቢ ጉዳይ የሆነውን የህክምና ባለሞያዎች የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ ይገኛል።

አብዛኛው ህዝባችን ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እያገኘ አይደለም። ለዚህ አንዱ እና ዋናው ምክንያት ደግሞ የሀኪሞች ቁጥር ከህዝብ ብዛት አንፃር አንስተኛ መሆኑ ነው። ይህ ሆኖ እያለ ብዙ ገንዝብ ወጥቶባቸው ረጅም እና ከባድ የሆነውን የህክምና ትምህርት ጨርሰው የተመረቁ ሀኪሞች ስራ አጥ ሁነው ተቀምጠዋል። ይህን ችግር በአጭር ጊዜ እና በዘላቂነት ለመፍታት የኢትዮጲያ ህክምና ማህበር ከጤና ሚንስቴር የክልል የጤና ቢሮዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ ይገኛል። ለምሳሌ መንግስት ለጤና የሚመድበው በጀት እና የጤና ተቋማት የሰራተኛ መደብ እንዲሻሻል በመረጃ ላይ የተመሰረተ ግፊት እና ምክረ ሃሳብ እያበረከተ ነው። ሀኪሞች በተናጥል ወይም በቡድን የራሳችውን ስራ መስራት እንዲችሉ እንደ Office Practice እና Physician Plaza ያሉ አዳዲስ አማራጭ መፍትሔዎችን በማቅረብ ስራው ለሚመራበት ደረጃ ዝግጅት ሙያዊ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል:: ከዚህ በተጨማሪም የውጭ ሀገር የስራ እድሎች እንዲመቻቹ ከጤና ውጭ ጉዳይ እና ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስትሮች እና የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ጋር እየሰራ ነው።

የሃኪሞችን ስራ አጥነት በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረገው ጥረት እንደተጠበቀ ሁኖ ጤና ሚንስቴር የወሰዳችው የአጭር ጊዜ የመፍትሄ እርምጃዎችም አሉ። ከነዚህም ውስጥ እንዱ ሃኪሞችን በኮንትራት መቅጠር ነው። ነገር ግን በኮቪድ-19 የህክምና ማእከሎች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚሰሩ ሀኪሞች ኮንትራት መቋረጥን አስመልክቶ በቅርቡ በድሬደዋ ደቡብ እና አማራ ክልሎች የተነሱ ቅሬታዎችን በተመለከተ እነኚህ የሀገር ባለውለታ ሀኪሞች ቋሚ የመንግስት ተቀጣሪ እንዲሆኑ ከጤና ሚንስቴር እና ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊዎች ጋር እየተመካከረ ይገኛል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ጤና ሚንስቴር ጥሩ የሆኑ ፈጣን እርምጃዎች ወስዷል:: ለገንዘብ ሚንስቴር ለፐብሊክ ሰርቢስ ኮሚሽን እና ለክልል ጤና ቢሮዎች የተፃፉ ደብዳቤዎችን በዋቢነት አያይዘናቸዋል። ሃኪሞችም ይህን ተገንዝባችው ስራችውን ተረጋግታችው እንድትሰሩ እና ከሙያ ማህበራችው ጋር በቅርበት በመመካከር ዘላቂ መፍትሄ አብረን እንድንፈልግ ጥሪ እናቀርባለን።