የአንድ ሳምንት የነጻ የጤና ምርመራ እና ህክምና አገልግሎት ከመቶ ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ሊሰጥ ነው።

“በጎነት ለጤናችን” በሚል መሪ ቃል መቶ ሺ ለሚሆኑ ዜጎች ከነሀሴ 16 እስከ 21 ቀን 2014 ዓ.ም ነጻ የጤና ምርመራ እና የህክምና አገልግሎት ዘመቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይሰጣል፡፡

በዚህ ዘመቻ የተጠናከረ የጤና አጠባበቅ ትምህርትና ምክር አገልግሎት በተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ፣የኮሌራና ሌሎች ውሀ ወለድ ተቅማጥ በሽታዎች፣ ወባ፣ ኤች አይ ቪ ፣ ቲቢ ፣ ኮቪድ-19፣ የካንሰር ህመምና ሌሎች ትኩረት በሚሹ የጤና ጉዳዮች ላይ ማለትም የደም ግፊት ፣የደም የስኳር መጠን፣ ከአንገት በላይ፣ የአይን፣ የቆዳ፣የስነ ምግብ፣ አእምሮ ጤና ሌሎችም የጤና አገልግሎቶች እንደሚሰጡም ዶ/ር ሊያ ታደሰ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

የነፃ የጤና ምርመራና ህክምና ዘመቻው በሀገር አቀፍ በጎ ፍቃደኛ ባለሙያዎች፣ የግል እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና የመንግስት ጤና ተቋማትን በማስተባበር ለማካሄድ በየደረጃው የዝግጅት ስራ እየተሰራ ይገኛል ያሉት ዶ/ር ሊያ ታደሰ በዚህ ዘመቻ ተደራሽ የሚሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም የመክፈል አቅም የሌላቸው አቅመ ደካማ ዜጎቻችን፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችና ሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰባችን ክፍሎች መሆኑን ተናግረዋል።

በምርመራው ወቅትም ተጨማሪ ከፍተኛ ህክምናና ምርመራ የሚያስፈልጋቸውን ወደ ሚመለከታቸው የጤና ተቋማት እንደሚላኩና ተጨማሪ አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚደረግ እንዲሁም ይህ ዘመቻ የጤና አገልግሎትን ከመስጠት ባለፈ የህዝባችንን የጤና ንቃት ለማሳደግና የመረዳዳት ባህላችንን የበለጠ ለማሳደግ የራሱ ከፍተኛ አስተዋጾ እንደሚኖረው ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡