ዶ/ር መረርቱ ተመስገን

ዶ/ር መረርቱ ተመስገንበተለያዩ የሥራ ሃላፊነቶች የላቀ አገልግሎት ተሸላሚ

የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር የቦርድ አባል የሆኑት ዶ/ር መረርቱ ተመስገን በኦሮሚያ ክልል በነቀምት ከተማ ተወለዱ፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኪዳነ ምሕረት ት/ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአ/አ ከተማ ቤተል መካነ ኢየሱስ ት/ቤት ተከታትለዋል፡፡
የመጀመሪያ የሕክምና ዲግሪያቸውን በጅማ ዩኒቨርስቲ፣ የህፃናት ህክምና ስፔሻሊቲ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል፡፡ እንዲሁም በህፃናት ድንገተኛና ፅኑ ህሙማን ህክምና ሰብ ስፔሻሊቲን በአሜሪካና በህንድ ሀገራት አጠናቀዋል፡፡

በአምቦ ሆስፒታል በጠቅላላ ሀኪምነት፣ በየካቲት 12 ሆስፒታል የሕፃናት ሕክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊና ምክትል ፕሮቮስት በመሆን አገልግለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ቦርድ አባል እንዲሁም የምስራቅ፣ የመካከለኛው እና የደቡብ አፍሪካ የህፃናት ህክምና እና የህፃናት ጤና ኮሌጅ የመስራቾች አባል ናቸው፡፡ በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በተባባሪ ኘሮፌሰር ማዕረግ በሕፃናት ሕክምና ሰብ ስፔሻሊስትነት እንዲሁም በመምህርነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

ካበረከቷቸው አስተዋፅኦዎች መካከልም የጤና ስርአት ተኮር የስፔሻሊቲ ትምህርት ማስፋፋትና ማጠናከር፣ የተለያዩ መመሪያዎችን ማዘጋጀት፣ የሕፃናት የሕክምና አገልግሎት የማሻሻያ ሥራዎች፣ በሕፃናት የቃጠሎ ሕክምና ሂደት፤ በህፃናት የላንቃ መሰንጠቅ የሕክምና አልግሎት አሰጣጥ እንዲሻሻል የሰሯቸው ስራዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በርካታ አጫጭር ስልጠናዎችን የተከታተሉ ሲሆን የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎችንም ሰርተዋል፡፡

በአቢሲኒያ የሊደር ሺፕ አዋርድ የተሰጣቸው እውቅናን ጨምሮ በርካታ እውቅናዎች ተበርክቶላቸዋል፡፡
ዶ/ር መረርቱ ተመስገን፤ በጤናው ዘርፍ በተለያዩ የሥራ ሃላፊነቶች የላቀ አገልግሎት ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅዎ ጤና ሚኒስቴር በ27ኛው የጤና ዘርፍ አመታዊ ጉባኤው ተሸላሚ በማድረግ መርጧቸዋል፡፡