ጥንቃቄ የሚያሻው 4ኛ ዙር የኮቪድ-19 ወረርሺኝ

ከሰሞኑ ጉንፋን መሰል በሽታ በሀገራችን ወረርሽኝ በሚመስል መልክ ተስፋፍቶ ብዙ ሰዎችን አጥቅቷል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ባለፉት 15 ቀናትም በሀገራችን በኮቪድ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሩዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት በአዲስ አበባ በቅርቡ ባደረገው የመስክ ናሙና ቅኝት በአንድ ሳምንት ውስጥ ወደ ጤና ተቋማት ሄደው የኮቪድ-19 ምርመራ ከተደረገላቸው 55562 ሰዎች ውስጥ 25191 ያህሉ ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጧል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃም ምልክቱም ታይቶባቸው የጤና ምርመራ ካደረጉ 83237 ሰዎች መካከል 29279 ያህሉ የኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ እንዲሁም 41 የሚሆኑ ሰዎች ከበሽታው ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን 260 የሚሆኑት ደግሞ በጽኑ ህሙማን ክፍል እገዛ እየተደረገላቸው ነው፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በየጊዜው በሚለቀው መረጃ መሰረት በ26-04-2014 እለት ብቻ 12951 ሰዎች ላይ በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ 4011 ያህል ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፤ 366 ሰዎች ደግሞ በጽኑ ታመዋል፡፡ እስካሁን በአጠቃላይ በሃገራችን 426656 ሰዎች ቫይረሱ ሲገኝባቸው 6981 ሰዎች በህመሙ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

በሀገራችን ከባለፈው ሁለት ሳምንት ጀምሮ የኮቪድ-19 የመስፋፋት ስርጭት መጠን በተከታታይ ጭማሪ እያሳየ ነው፡፡ ይኸውም ከጥቂት ሳምንት በፊት 5 በመቶ ብቻ የነበረው የመስፋፋት መጠን አሁን ወደ 36 በመቶ ደርሷል፡፡

ስለሆነም ማህበረሰቡ የኮቪድ-19 የመከላከያ መንገዶችን ማለትም

  1. ማስክን ሁሌም በአግባቡ መጠቀም
  2. ርቀትን መጠበቅ
  3. እጅን በሳሙና መታጠብ ወይም በአልኮል ማጽዳት እና
  4. ሌሎች የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያወጣቸውን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረግ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው፡፡

የኮቪድ-19 ምልክቶችን ሲያዩ ማለትም ፡ የንፍጥ መዝረብረብ፣ ራስ ምታት፣ድካም፣ የመገጣጠሚያ እና ወገብ ህመም፣ ሳል ሲያዩ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ አፋጣኝ ምርመራ በማድረግና፤ በቫይረሱ መያዝዎ ከተረጋገጠ ደግሞ በቤት ውስጥ እራስን በመለየት መቆየት ብሎም የኮቪድ-19 ክትባትን በአቅራቢያዎ በሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ መከተብ ይኖርብዎታል፡፡

የመንግስትና የግል ተቋማት ትምህርት ቤቶች እና ሌሎችም ተቋዋማት የኮቪድ-19 የመከላከያ መንገዶችን በጥንቃቄና ሳያሰልሱ መጠቀም በሽታው እያደረሰ ያለውን ችግር ለመቀነስ ብሎም ወደፊት የሚያደርሰውን አደጋ ለመግታት ወሳኝ እርምጃ ነው፡፡