ዶ/ር ሰለሞን ቡሣ

ዶ/ር ሰለሞን ቡሣ በዓይን ህክምና በስፔሻሊስት ደረጃ ሰልጥነው ከ1958 ዓ.ም አንስቶ ለ46 ዓመታት በተለያዩ ሀገሪቱ ተቋማት ማህበረሰቡን አገልግለዋል፡፡

የአለርት ሆስፒታልን ከሶስት ዓመታት በላይ በሜዲካል ዳይሬክተርነት የመሩ ሲሆን በዚህ ቆይታቸው ቁጥራቸው በርከት ያሉ ሀኪሞች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስፔሻላይዜሽን ኘሮግራም እንዲያመሩ በማገዝ፣ ከጤና ሚኒስቴር ባገኙት ድጋፍና መመሪያ በአለርት ሆስፒታል የድንገተኛ ህክምና ማዕከል እንዲቋቋም በማድረግ፣ ከውጪ አጋር አካላትን በማስተባበር ከፍተኛ የዋጋ ግምት ያላቸው የዓይን ህክምና መሣሪያዎችን በማስገባት ተገልጋዮች መፍትሄ እንዲያገኙ በማድረግ በኩል የመሪነት ሚናቸውን ተወጥተዋል፡፡
ዶ/ር ሰለሞን የዓይን ህክምና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንዲስፋፋ ለማድረግም ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡

በተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ፣ የግል የጤና ኮሌጆችና ማሰልጠኛዎች፣ እንዲሁም በሚያገለግሉበት የአለርት ሆስፒታል የዓይን ህክምና ባለሙያዎች የተሻለ ስልጠና አግኝተው አይነስውርነትን እንዲከላከሉ ዕውቀታቸውን ለብዙዎች አጋርተዋል፡፡ በደብረብርሃን፣ በአምቦ፣ በወረኢሉ፣ በዶዶላ፣ በመካነሰላም፣ በግንደበረትና በአጣጥ ሆስፒታሎች በዓይን ሞራ (ካታራክት) የሚሰቃዩ ዜጎች ህክምና እንዲያገኙ በማድረግና ስራውም ዘለቄታ እንዲኖረው ከፍተኛዉን ሚና ተወጥተዋል፡፡
ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ የአለርት ሆስፒታል ህክምና ክፍል ኃላፊ ሆነው ያገለገሉት ዶ/ር ሰለሞን በቅርቡ በጦርነት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት የተለያዩ ድጋፎች እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡ የጤና ሚኒስቴር የዘንድሮው ዓመት የህይወት ዘመን የላቀ የሙያ አገልግሎት ተሸላሚ እንዲሆኑ መመረጣቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያረጋግጣል፡፡