“ሃኪሞች መሪነትን እየተማሩ የመጪው ጊዜ ሀገር ተረካቢዎች መሆን ይኖርባቸዋል ብዬ አምናለሁ”
ዶ/ር ደምመላሽ ገዛኸኝ

ዶ/ር ደምመላሽ ገዛኸኝ ይባላል፡፡ በጥቁር አንበሳ እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የድንገተኛና ጽኑ ህሙማን እስፔሺያሊስት ነው፡፡ አሁን ደግሞ በቂሊንጦ የመከላከያ ሰራዊት ማገገሚያ ማዕከል ሜዲካል ዳይሬክተር፡፡ ከሱ ጋር ስለ አንዳንድ ነገሮች ቆይታ አድርገናል፡፡

ጥያቄ፡ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር አባል መቼ ሆንክ ?

በ 2016 እንደ እ.ኤ.አ አቆጣጠር ከተመረቅን በኋላ በመጀመሪያ ያደረጉት ወደ ማህበሩ ሄጄ ቢሮዉን ማየት ነበር፡፡ የሚሰራውን ስራ፡ በተለይም የያዘውን ቦታ ካየሁ በኋላ ማህበሩ በጣም ትልቅ አቅም እንዳለው ተረዳሁ፡፡ ተማሪ እያለሁም አመታዊ ስብሰባዎችን እሳተፍ ነበር ልክ ስመረቅ አባል መሆን እንዳለብኝ ወስኜ ነበር፡፡ ከምጠብቀውም በላይ ሆኖ ስላገኘሁት ገርሞኝ ነበር፡፡

ዶ/ር ደምመላሽ ገዛኸኝ

ጥያቄም አጭሮብኝ የነበረው ነገር ለምን ይህን ያህል ቦታ የዞ ህንጻ አልሰራም የሚለው ጥያቄ ነበር፡፡ ማህበሩ ስሙ ትልቅ ነው፡፡ በብዙ የህክምና ሰዎች አእምሮ ውስጥ አለ፡፡ በርግጥ በወቅቱ የነበሩት አሳሪ ህጎች ማህበሩ ላይ ትልቅ ተጽእኖ ነበራቸው፡፡ ከዚህም በላይ ማህበሩ ትልቅ ስም ያለው የህክምና ጆርናል ያሳትማል፡፡ እኔ በበኩሌ የራሴን ጥናት ልኬም ነበር በአንድ አንድ ምክንያቶች ሳይታተም ቢቀርም፡፡ ለማንኛውም ከ 2016 ጀምሮ በማህበሩ ውስጥ በንቃት ተሳትፎ አድርጌያለሁ፡፡

ጥያቄ፡ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበርን በህክምና ሞያ ውስጥ ላሉ ሰዎች ያለውን ፋይዳ እንዴት ትገልጸዋለህ ?

መሰረታዊ የሞያ ማህበራት አላማ የባለሞያውን መብት ማስጠበቅና ሞያው እንዲያድግና ማህበረሰቡም ማግኘት ያለበትን ጥቅም እንዲያገኝ ማድረግ ነው፡፡ ማህበሩ ከዚህ አንጻር ምን አድርጓል ምን ማድረግ ይችል ነበር ብለን ብንጠይቅ ጥሩ የመስለኛል፡፡ ከዚህ አንጻር እኔ እንደምሳሌ የምጠቅሰው ኮስት ሼሪንግን በተመለከተ የህክምና ተመራቂ ተማሪዎች እስከ 427 ሺ ብር ካልከፈሉ ዲግሪያቸውን መውሰድ እንዳይችሉ የሚል ህግ ወጥቶ ነበር፡፡ ይህን ኢ-ፍትሃዊ ህግ ለማስቀረት ማሕበሩ ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርግ ነበር፡፡ በተለይም በወቅቱ የነበሩት የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገመቺስ ማሞ በጣም ጉዳዩን ሲከታተሉ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በ 2019 በነበረው  የሃኪሞች እንቅስቃሴ ጉዳዩ ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡ ነገር ግን ማህበሩ ያኔ ካደረገው አስተዋጽኦ በላይ ጉዳዩን በመሪነት በመያዝ በመምራት፤ለሞያተኞች ተገን በሞሆን የተሻለ አስተዋጽኦ በማድረግ ተቀባይነቱን አሁን ካለው በላይ ማስፋት ይችል ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡

እኔም እንደሚገባኝ የሞያ ማረጋገጫን ለምሳሌ የጤና ሚኒስቴርና  የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ናቸው እየሰጡ ያሉት፡፡ ነገር ግን ያደጉት ሃገራት ተመክሮን በመከተል የሞያውን ጉዳይ ለባለሞያው ነው መተው ያለበት፡፡ ማህበሩ እነደዚህና መሰል ጉዳዮችን ወደራሱ በማዞር ትልቅ ስራ መስራት አለበት፡፡ ጅምር ስራዎች ቢኖሩም የበለጠ ተጠናከሮ መሰራት ያለበት ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ሌላው medico-legal ጉዳዮች ላይ መስራት ቢቻል ጥሩ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ የሃኪሙን ስም የሚያጠለሹ ጉዳዩች ብዙ ጉዳት ካደረሱ በኋላ ነው እልባት የሚያገኙት፡፡ እንዲህ አይነት ጉዳዮችን ማህበሩ ቢሰራባቸው የሃኪሙን ጥቅም ከማስጠበቅም ባሻገር ለማሕበረሰቡም ግንዛቤውን እንዲያሰፋ ያግዝ ነበር፡፡ በእርግጥ  የገንዘብ ችግር ማነቆ ሊሆን እንደሚችል እረዳለሁ፡፡ ይኹንና ገንዘብ ማግኛ ምንጮችን ለምሳሌ የአባላት መዋጮን በማስፋት እና ሌሎች የገንዘብ ማግኛ አማራጮችን በማስፋት የሚጠበቅበትን ድርሻ መወጣት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡

ጥያቄ፡ ወደፊት ስለ  በኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ላይ ምን ተስፋ ታደርጋለህ ምን ትመኛለህ ?

የመጀመሪያው ነገር ሃኪሞች መሪነትን እየተማሩ የመጪው ጊዜ ሀገር ተረካቢዎች መሆን ይኖርባቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ማህበሩ የተሟላ ተቀጣሪ ያስፈልገዋል፡፡ ሁለተኛ አሁን ያለውን ቦታ በማልማት ትልቀ ተቋም  መሆን ይችላል፡፡ የያዘው ቦታ ትልቅ አቅም ስለሆነ ታቅዶበት ሊሰራ ይገባል፡፡

ከጤና እና ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመነጋገርማስከበር ያለበት ድርሻ አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ ላይሰንስ መስጠትም ሆነ መንጠቅ፡ medico-legal ጉዳዮች ላይ በንቃት መሳተፍ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህም ባለፈ የጤና ባለሞያዎችን መብት በማስጠበቅ ላይ በጥልቀት ቢሰራ ብዬ እመኛለሁ፡፡ ይህን በማድረግ በአዳዲስ የሙያው ባለቤቶች ዘንድ ያለውን ስምና ተቀባይነት ማሳደግ ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይ በቅርብ ጊዜ በኢንተርኔት በተለይም በሶሻል ሚዲያ ላይ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው፡፡ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

ጥያቄ፡ አሁን ባለህበት ቦታ ተመድበህ ስትመጣ ምን ተሰማህ እንዴት አገኘኸው ?

ወደዚህ ቦታ ማለትም በቂሊንጦ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ማገገሚያ በሜዲካል ዳይሬክተርነት ተመድቤ ስመጣ ከዚያ በፊት ኢመርጀንሲ ላይ እሰራ ስለነበር ያን ያህል አልከበደኝም፡፡ በስራው የተጨናነቀ ሁኔታን ማየት የተለመደ ነው፡፡ በኢመርጀንሲ ክፍል ውስጥ አስቸኩዋይና ወሳኝ የሆነ እርምጃ መውሰድ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ባለፈውም ጦርነቱ እንደተጀመረ ሰሞንም መቀሌ ሰርቼአለሁ፡፡ እዛ መስራቴ ላሁኑ ስራዬ አግዞኛለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡

ወደ እዚህ ስመጣ ባዶ አዳራሽ ነበር፡፡ ህዝቡ ተረባርቦ በመንግስትም እገዛ እንዲሁም ማህበራት ለምሳሌ የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር ባደረጉት እገዛ በሁለት ሳምንት ውስጥ ስራ ለመጀመር ችለናል፡፡ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ህመምተኛ በብዛት መምጣቱ ትልቅ ጫና ይፈጥር ነበር፡፡ ይሁንና ባለሞያው በትልቅ ቁርጠኝነት ለረጅም ሰዓታት በመስራት የነበረውን መጨናነቅ ለመወጣት ችለናል፡፡

የባለሞያና የመድሃኒት እጥረቶችም ነበሩ፡፡ እሱንም በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ፡ ባለሃብቶች፤ የአቃቂ ክፍለ ከተማ አመራሮች እና የተለያዩ ማሕበራት የኢትዮጵያ ህክምና ማህበርን ጨምሮ ባደረጉት ርብርብ ችግሩን ቀርፈን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡

ጥያቄ፡ የህክምና ሰዎች ተሳትፎ እንዴት ታየዋለህ ?

ሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋ ከህክምና ጋር ተለያይተው አያውቁም፡፡  የሀገራችንም ሆነ የዓለም አቀፍ ታሪክም እንደሚያሳየው የህክምና ሚና በጦርነትም ሆነ በአደጋ ጊዜ የጎላ ነው፡፡

በዚህ ሰዓት በደብረብርሃን በወልዲያ እዚህም በአዲስ አበባ የህክምና ባለሞያዎች በፍቃደኝነትም ሆነ በምደባ ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ስራ እየሰሩ ነው፡፡ እንኳንስ በእንደዚህ አይነት ሀገራችን በምትፈልገን ወቅት ይቅርና በሰላሙም ወቅት ከ አንድ ሺ በላይ ሰው ሲሰበሰብ አስፈላጊወን ጥንቃቄ እና አሰራር በመከተል ሀኪሞች ግዴታቸውን ይወጣሉ፡፡ በአንዳንድ የጦርነት ቀጠናዎች የህክምና ባለሞያዎች እራሳቸውን አደጋ ላይ አጋልጠው የሞያ ግዴታቸውን የተወጡበት ሁኔታ ነበር፡፡

ከራሴ እንኳን ብጀምር ለዚህ ቦታ ስመደብ ድንገት ነው፡፡ ያለውን ነገር ነገሩኝ እናም አሁን ባለሁበት ቦታ ልንመድብህ ነው አሉኝ፡፡ ምንም አላቅማማሁም ቀጥታ ወደ ስራ ነው የገባሁት፡፡ ለሀገርና ለህዝብ የሚከፈል ዋጋ ስለሆነ፡፡

ጥያቄ፡ የሞያ ማህበራትንስ አስተዋጽኦ እንዴት ትገልጸዋለህ ?

አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር በጣም ትልቅ ስራ እየሰራ ነው፡፡ ማህበሩያወጣውን የነፃ አገልግሎት ጥሪውን አይቼዋለሁ፡፡ ተመዝግበውም የተመደቡ ባለሞያዎች እንዳሉ መረጃው አለኝ፡፡ እኛም ጋር ሶስት ጄኔራል ፕራክቲሽነርስ ማህበሩ ባወጣው ጥሪ ተመዝግበው የመጡ አሉ፡፡ እንደሚገባኝ አሁን የፈለግነው ቁጥር ይኼ ስለሆነ ነው እንጂ ብዙ ብንፈልግ ማህበሩ ብዙ ሊያቀርብልን ይችል ነበር፡፡

በ ሀገር አቀፍ ደረጃ እተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ቀላል አይደለም እያደገ የሚሄድና የሚጎለብት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር አስተዋጽኦ በተለያዩ ዘርፍ ማደግ አለበት የሚፈጥረው ተቀባይነት ቀላል አይደለም፡፡

ከመንግስትና ከሌሎች የሞያ ማህበራት ጋር መስራት ቀላል አይደልም፡፡ ከዛም ባሻገር የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ሰራተኞች የደሞዛቸውን 50 በመቶ አዋጥተው ለዚህ ለቂሊንጦ ማገገሚያ መድሃኒት በመግዛት አበርክተዋል፡፡ በጣም ደስ የሚል ነገር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተግባር ይግዛውን ጋብዘን እዚሁ መጥተው በጣም አመርቂ የሆነ ውይይት አድርገናል፡፡

ጥያቄ፡ የሚቀር የምትለው ነገር ካለ ?

እንደሚታወቀው አሁን እንደሀገር ያለንበት ሁኔታ ትንሽ አስቸጋሪ ነው፡፡ ጦርነቱ በሽታው በተለይ የኮቪድ 19 እና መሰል ተግዳሮቶች እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ማህበረሰብ እየፈተኑን ነው፡፡ እንደ ማህበረሰብ ከዚህ ለመውጣት የምናደርገውን ጥረት አይቶ ፈጣሪ በምህረቱ ያስበን እላለሁ አመሰግናለሁ፡፡