በኮቪድ 19 ክትባት ዙሪያ የግንዛቤ እና የአመለካከት ክፍተቶች ላይ ለመስራት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ::

የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ እና ከፒኤስ አይ ኢትዮጵያ ጋር በትብብር በመሆን የኮቪድ 19 ክትባትን አስመልክቶ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ የሜዲካል ዳይሬክተሮችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የእናቶችና ህጻናት ዳይሬክተር ወ/ት ስንዱ መኩሪያ በመክፈቻ ንግግራቸው የኮቪድ 19 ክትባትን አስመልክቶ እንደ አዲስ አበባ ጤና ቢሮ ባሉት የጤና ተቋማት ክትባቶችን ታላሚ ለተደረጉ የሕብረተሰብ ክፍሎች እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አክለውም በአገር አቀፍ ደረጃ ሶስት የክትባት ዘመቻዎች መካሄዳቸውን አስታውሰው በኮቪድ 19 ክትባት ዙሪያ ያሉ የግንዛቤና የአመለካከት ክፍተቶች ላይ በተገቢው መንገድ በመስራት የማህበረሰባችንን ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ ብሎም ለመታደግ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር ኤክኪዩቲቭ ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት መኮንን በበኩላቸው ማህበሩ በህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ፣ በታካሚዎች ደህንነት እና በአጠቃላይ በህክምናው ዘርፍ ቁልፍ ሚና በመጫወት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ኮቪድ 19 በሃገራችን ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን ጠቃሚ ተግባራት ሲያከናውን የቆየ መሆንን አስታውሰው ወደ ክትባቱ ሲመጣም የተጀመሩ ስራዎችን በማስቀጠል የበኩል መወጣቱን አስረድተዋል፡፡ በቀጣይም ይህንኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

የኮቪድ 19 እያደረሰ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እና የኮቪድ 19 ክትባት እውነታዎች እንዲሁም ማህበረሰቡ በክትባቱ እምነት ኖሮት እንዲከተብ መሰራት ስለሚገባቸው ስራዎች ዙሪያ ልዩ ልዩ ጽሁፎች ቀርበው በዕለቱ በተገኙ ታደሚዎች ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

ጽሁፍ አቅራቢዎች በበኩላቸው በኮቪድ 19 ክትባት ዙሪያ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለማስወገድ ከባለሙያው ጀምሮ በተገቢው መንገድ የግንዛቤ ስራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አንስተው በታዳሚዎች ለተጠየቁ ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡