ዶ/ር ኮከብ መሐመድ


የህይወት ዘመን የላቀ የሙያ አገልግሎት ተሸላሚ

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ በደደር ወረዳ ተወለዱ፡፡ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጅማና በአዲስ አበባ ተምረዋል፡፡ የህክምና ዲግሪያቸውን ከጎንደር ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኙ ሲሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ደግሞ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡

ከ38 ዓመት በላይ በተሻገረው የስራ ልምዳቸው በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህር፤ በህይወት ፋና ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ህክምና ክፍል ኃላፊ፤ በደደር ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር፣ በሐረር ጀጎል ሆስፒታል፤ በፖሊስ ሆስፒታልና በሐረር ጦር ኃይሎች ሆስፒታል በባለሙያነት እና በኃላፊነት ያገለገሉ ሲሆን በተለያዩ ሆስፒታሎችና የህክምና ኮሌጆች ሃላፊና የቦርድ ሰብሳቢ በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በሀገር ውስጥና በውጭ ሃገራት በርካታ ስልጠናዎችን የወሰዱ ሲሆን የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ሰርተዋል፡፡

በምስራቅ ኢትዮጵያ የመካንነት ችግርን ለመቅረፍ እና የእናቶችን የመውለድ ጥያቄ ለመመለስ የበኩላቸውን አስተዋፅዎ አድርገዋል፡፡ በዚህም ከ15,880 በላይ እናቶች ልጅ ወልደው እንዲስሙ ሙያዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል፡፡

ዶ/ር ኮከብ መሐመድ፤ በጤናው ዘርፍ በህይወት ዘመን ላበረከቱት የላቀ የሙያ አገልግሎት ጤና ሚኒስቴር በ27ኛው የጤና ዘርፍ አመታዊ ጉባኤው ተሸላሚ በማድረግ መርጧቸዋል፡፡