ዶ/ር ፈቀደ አግዋር

ልዩ ተሸላሚ

በአዲስ አበባ ከተማ መሳለሚያ፤ አማኑኤል ሆስፒታል አካባቢ ነው የተወለዱት፡፡ የ1ኛ እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሰላም በር አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እና በአዲስ ከተማ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትለዋል፡፡

የመጀመሪያ የህክምና ዶክትሬት ዲግሪያቸውን የጎንደር ህክምና ሣይንስ ኮሌጅ ያገኙ ሲሆን የአጠቃላይ ቀዶ ጥገና ትምህርታቸውን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተከታትለዋል፡፡ የልብ ቀዶ ጥገና ሰብ ስፔሻሊቲ ትምህርታቸውን ደግሞ በህንድ አገር ተምረዋል፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በፊዚዮሎጂ መምህርነት እና በቀዶ ጥገና ረዳት ፕሮፌሰርነት አገልግለዋል፡፡ በደምቢ ዶሎ ሆስፒታል የአጠቃላይ የቀዶ ጥገና ሐኪም በመሆን ያገለገሉ ሲሆን አሁን ድረስ በኢትዮጵያ የልብ ህክምና ማዕከል የአዋቂዎች እና የህፃናት የልብ ቀዶ ጥገና ሐኪም ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡

በሀገራችን የመጀመርያውን ልብና ሳንባን ተክቶ የሚሰራ ማሽንን በመጠቀም (Heart Lung Machine) የልብ ቀዶ ጥገናን አስጀምረዋል፡፡ ዛሬ ላይ ከ1000 የሚበልጡ ጨቅላ ህፃናትና አዛውንቶችን የተሳካ የልብ ቀዶ ጥገናዎችን ሰርተዋል።

በሚሰሯቸው ቀዶ ጥገናዎች ላይ በማተኮርም ከ15 ያላነሱ ሳይንሳዊ የምርምር ፁሑፎችን በመጻፍ በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል። “የልብ ጠጋኙ ማስታወሻ” በሚል ርዕስም በአማርኛና በእንግሊዘኛ መጽሐፍ ጽፈው አበርክተዋል።

በሀገራችን የተንሰራፋውን የRheumatic የልብ በሽታ ጫና ለመቀነስ ሂሊንግ ቫልቭስ ኢትዮጵያ የሚል ግብረ ሰናይ ድርጅት አቋቁመው ከፍለው መታከም የማይችሉ ታዳጊ ህመምተኞችን ቀዶ ጥገና እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ አሁን ላይም ለ40 ታዳጊዎች የነፃ የልብ በር ቀዶ ጥገና አድርገዋል።

ዶ/ር ፈቀደ አግዋር፤ በጤና ሙያ መስክ ላበረከቱት የላቀ ልዩ ስራና የሙያ አገልግሎት ጤና ሚኒስቴር በ27ኛው የጤና ዘርፍ አመታዊ ጉባኤው ልዩ ተሸላሚ በማድረግ መርጧቸዋል፡፡