በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሕክምና ትምሕርት ቤት፣ የራዲዮሎጂ ትምሕርት ክፍል ባልደረባ የነበሩት ፕሮፌሰር አስፋው አጥናፉ፣ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ዓርብ ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም አርፈዋል፡፡
ፕሮፌሰር አስፋው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ፋከልቲ፣ የሕክምና ዶክትሬት ዲግሪያቸውን በ1976 ዓ.ም አግኝተዋል፡፡
በአጠቃላይ ሐኪምነት አሰብ ሆስፒታል ካገለገሉ በኋላ በራዲዮሎጂ ስፔሽያሊቲ ትምህርት ከመጀመሪያ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች አንዱ በመሆን በ1981 ዓ.ም ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ እንዲሁም በ2006 ዓ.ም በቦዲ ኢሜጂንግ ሰብ ሰፔሺያልቲ ፕሮግራም ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ተመራቂዎች መካከል አንዱ በመሆን አጠናቀዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ በሰላሳ አምስት ዓመት የዩኒቨርሲቲ የአገልግሎት ዘመናቸው ብዙ ኃላፊነቶችን ተወጥተዋል፡፡ ለአራት ተርም በራዲዮሎጂ ዲፓርትመንት ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከሰሜን አሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትበብር በመፍጠር በትምህርት ከፍሉ የተለያዩ የሰብ ሰፔሻልቲ ትምህርቶች እንዲጀመሩ አድርገዋል፡፡
የራዲዮሎጂ ቴክኖሎጂ ትምህርት በባችለር ዲግሪ እንዲሰጥ በማስቻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሲሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ የቴሌ ሜዲስን ዩኒት፣ በቀጣይም የኢ-ሄልዝ ማዕከል እንዲቋቋም ያደረጉ ሲሆን በኃላፊነት ደረጃም ሰርተዋል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ራዲዮሎጂ ማህበርን ለመመሥረት ሃሳብ ከማመንጨት ጀምሮ ከመስራቾቹ አንዱ በመሆን የመጀመሪያ የማሕበሩ ፕሬዚደንት ሆነው አገልግለዋል፡፡
ከሰላሳ አምስት በላይ የጥናት ጽሑፎችን ያሳተሙ ሲሆን ባደረጓቸው ጥናቶች በማስተማር፣ በጤና አገልግሎት፣ በማሕበረሰብ አገልግሎት እና በአጠቃላይ በዩኒቨርስቲው ሆነ በሐገር፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ባበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በ2010 ዓ.ም የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ በተጨማሪም፣ የተለየያዩ አገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል፡፡
ፕሮፌሰር አስፋው ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ነበሩ፡፡
ሥርዓተ ቀብራቸውም ዛሬ፣ ግንቦት 12 ቀን 2016 ከቀኑ 6፡00 ሰዓት በመካኒሳ አቦ ቤተ ክርስቲያን ይፈጽማል። የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር በፕሮፌሰር አስፋው ህልፈተ ሕይወት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለፀ ለቤተሶቦቻቸው እና ወደጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ይመኛል፡፡